ጀምበሬ ሃይሉ
ቀኝ ጌታ ጀምበሬ ኃይሉ ደብረ ታቦር ውስጥ ተወለዱ። በልጅነታቸው በቤተ ክርስቲያን ትምሕርት ዳዊት፣ ጾመ ድጓ፣ ቅኔ፣ ዝማሬ እና አቋቋም ያጠኑት እኒህ ሰው አሁን የሚታወቁት በስዓሊነት ነው።
በ፲፱፻፲፱ ዓ/ም ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ የወጣቱ ጀምበሬን አጎት ዓለቃ ዓለሙን ወሎ ውስጥ የምትገኘውን ተድባባ ማርያም የተባለች ቤተ ክርስቲያን በስዕል እንዲያስጌጡ ጠየቋቸው። በዚህ መሠረት ወጣቱ ጀምበሬ አጎታቸውን በረዳትነት ተከትለው ወደ ወሎ በመሄድ የሥነ ስዕልን ጥበብ ተማሩ።
ከዚህ በኋላ የበጌምድር ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ እና የንግሥት ዘውዲቱ ባል የነበሩት ራስ ጉግሳ ወሌ ፣እናቲቱ ማርያም የተባለችውን የደብረ ታቦር ከተማ ቤተ ክርስቲያን በስዕል እንዲያስውቡ አዘዙ። ከሌሎች ሶስት ሰዓሊወች ጋር በመሆን ግዴታቸውን ፈጸሙ። ራስ ጉግሳ ወሌ ከሞቱ በኋላ የጠቅላይ ግዛቱ አስተዳዳሪ የነበሩት (በኋላ ከወንድማቸው ከደጃዝማቾች አበራ ካሳ ጋር እጃቸውን ለጠላት ሰጥተው የተገደሉት)ደጃዝማች ወንድወሰን ካሳ ቤተመንግሥታቸውን በስዕል እንዲያሸበርቁላቸው ጀምበሬን ጠይቀው ሥራው ሲጠናቀቅ ቀኝ ጌታ ጀምበሬን የጸሐፊነት ሥራ ሰጧቸው።
ከመጀመሪያ ሚስታቸው ጋር በ፲፱፻፳፭ዓ/ም ጋብቻ የፈጸሙት ጀምበሬ የመጀመሪያ ልጃቸውን ጦቢያ ጀምበሬን በ፲፱፻፳፯ ዓ/ም ላይ አገኙ። ወዲያው በዓመቱ ፋሽስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን ሲወር ከወታደር አባታቸው ጋር ወደማይጨው ጦርነት ዘመቱ። ከዚያም ጦርነት በኋላ ጠላት በ፲፱፻፴፫ ዓ/ም ለቆ እስከወጣ ድረስ ለአምሥት ዓመታት በአርበኝነት ተሳተፉ። ከነጻነት መልስ በኋላ ለአምሥት ዓመታት በስዕል ሥራ ተሰማርተው ከቆዩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ወዲያው ከንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መሬትና ቤት አገኙ።
አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት የስዕል ሥራቸው ከሚታይባቸው፣ እንጦጦ ማርያም እና ቀራንዮ መድኅኔ ዓለም ይጠቀሳሉ። በግላቸውም በመሳል ብዙ ሥራወችን ለሽያጭ አቅርበዋል። [1]
ማጣቀሻ[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
- ^ Silverman, Raymond A. "Jembere Hailu." Ethiopia: Traditions of Creativity. 1998.
No comments:
Post a Comment