ከዮሴፋዊ ዕጣ ፋንታ ወደ ቃየናዊ ዕይታ
ከያዕቆብ ልጆች መካከል፤ አንዱ ዮሴፍ የሚባል ነበር፡፡ ዮሴፍ፤
ወላጆቹ ያከብራል፤ ይወዳልም፡፡ የልጅ ግዴታውም ይወጣል፡፡ ዮሴፍ ለወንድሞቹም፤ ወንድማዊ ፍቅሩ ይለግስላቸዋል፡፡ እንዲሁም ያከብራቸዋል፡፡
እሱም ከወንድሞቹ የሚጠብቀው ወንድማዊ ፍቅርና ክብር ነው፡፡ ከክፉ ነገር እንዲጠብቁት ነው፡፡ የያዕቆብ ልጆች ግን በወንድማቸው
በዮሴፍ ላይ ቅናት ተጠናወታቸውና በወንድማቸው ላይ ተነሱ፤ ዮሴፍን ለመግደል ተመካከሩ፡፡ ዮሴፍ ከወንድሞቹ አንዱ በሆነ በሮቤል
ምክንያት ከሞት ተረፈ፡፡ ነገር ግን ሮቤል ወንድሙን ዮሴፍን በወንድሞቹ ከተጠነሰሰበት ሌላ ተንኮል አላስተረፈውም፤ ከመሸጥ፡፡ ወንድሞቹ፤
ዮሴፍን ለመንገደኞች በሃያ ብር ሸጡት (ዘፍ፥፴፯፤፳-፳፰)፡፡
የዚህ ዓይነት ድርጊት የዛሬ አንድ መቶ ሀያ ዘጠኝ ገደማ በጥቂት
የኢትዮጵያ ልጆች በኢትዮጵያ ምድር ተፈጸመ፡፡ አጼ ዮሐንስ ከሞቱ በኋላ፤ ምኒልክ የንጉሠ ነገስትነት ህልማቸው እውን ሆኖላቸው፡፡
ነገር ግን የትግራይ መሳፍንት ከውጭ ጠላትና የእርስ በእርስ በማያበራ ጦርነት ምክንያት ቢዳከሙም፤ የትግራይ መሳፍንት እርስ በእርስ
ከተባበሩ፤ የወደፊት የስልጣን ተቀናቃኝ እንደሚሆኑ ለምንሊክና ግብረ አበሮቻቸው የተሰወረ አልነበረም፡፡ በመሆኑ፤ ምንሊክ ንጉሠ
ነገሥት ከመሆናቸው በፊት ትግራይ ትግርኝ ማዳከም ነበረባቸው፡፡ ይህ እውን ሊሆን የሚችልበት ከተዘየዱ ሰይጣናዊ ዘዴዎች አንዱ፤
ትግራይ ትግርኝ ለሁለት በመክፈል፤ ከመረብ ወዲያ ያለ ህዝብ ለጣልያን መሸጥ ነው፡፡ ኤርትራውያን ከወንድሞቻቸው ነጥለው ለመሸጥ፤
ሚያዝያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም ‘ውጫሌ’ በተባለ ቦታ ከጣልያን ጋር ለድርድር ተቀመጡ፡፡ ኤርትራውያን፤ በጥቂት ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው
በጥቂት ሊሬ ተሸጡ፡፡
የያዕቆብ ልጆች ስለዮሴፍን መጥፋት (የዮሴፍ መሸጥ ወንድሞቹ
ብቻ ነው የሚያውቁት) አባታቸውን ሲነግሩት፤‘…ያዕቆብ ልብሱን ቀደደ፤ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ብዙ ቀን አለቀሰ’ (ዘፍ፥፴፯፤፴፬)፡፡
ይህ ድርጊት ዮሴፍም ለወደፊት ብርታት ቢሆንበትም፤ ለግዜው ግን ጨልሞበታል፡፡ ሆኖም ግን የዮሴፍ መሸጥ ለያዕቆብ ልጆች ደስታና
ፌስታ ነበረ፡፡ የኤርትራና የኤርትራውያን መሸጥ ለኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ከባድ ሐዘን ሆነ፡፡ ኤርትራውያንን ተዋውለው
የሸጡ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ግን የደስታ ግዜ ሆኖላቸው፡፡
ዛሬ ደግሞ ይባስ ብሎ፤ የትግራይ ህዝብ፤ ጥቂት ኢትዮጵያውያን
በቃየናዊ አተያይ እየተመለከቱት ነው፡፡ አቤል ከወንድሙ ከቃየን የተለየ ጥቅም ከማንም ባያገኝም፤ ቃየን ግን ወንድሙ አቤልን ‘ከእኔ
በላይ የእግዝሔር በረከት አገኘ’ በማለት በሰይጣናዊ ቅናት ተቃጠለና ወንድሙን አቤልን ሞት ተመኘለት፡፡ ቃየን፤ የገዛ ወንድሙን
ራሱ ገደለ (ዘፍ፥፬፤፬-፰)፡፡ ዛሬ የትግራይ ህዝብ፤ ከኢትዮጵያውያን ሁሉ ልዩ ተጠቃሚ አድርጎ በማሰብ፤ ጥቂት ኢትዮጵያውያን በቃየናዊ
አተያይ እየተመለከቱት ነው፡፡
እነዚህ በቃየናዊ መንፈስ የሚነዱ ጥቂት ኢትዮጵያውያን፤ የኢትዮጵያ
ህዝብ በወንድሞቹ በትግራይ ህዝብ እንዲነሣ ይሰብካሉ፡፡ እነዚህ ቃየናዊ አስተሳሰብና አመለካከት ያላቸው ጥቂት ኢትዮጵያውያን፤ ሌላው
የኢትዮጵያ ህዝብ በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት /genocide/ ተግባር እንዲፈጽም ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪ ያቀርባሉ፡፡ በትግራይ
ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ጥሪ ካቀረቡ ግለሰቦች የተወሰኑትን እንጥቀስ፡፡
በመጀመርያ፤ “አስኳል” የተባለው የአቶ እስክንድር ነጋ ጋዜጣ
በ1996 ዓ.ም በተክታታይ ያትም በነበረው‘ወግድ ይሁዳ’ በሚል ተከታታይ መጣጥፍ የትግራይ ህዝብ ለማጥፋት ለሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር
ብሔረ ሰቦች ያቀረበው የዘር ማጥፋት ጥሪ እንመለከታለን፡፡ የአስኳል ጋዜጣው መጣጥፍ፤ በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ናዚስቶች በአይሁዶች
ላይ የወሰዱት እርምጃ እንደአብነት በመጠቀም ሰፊ ሐተታ ያቀረበ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በወንድሞቹ በትግራይ ህዝብ ላይ ተመሳሳይ
ድርጊት እንዲፈጽም እንዲህ ሲል ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ‘የጀርመን ህዝብ በቆራጥነት ተነሥቷል፡፡ … መርዘኛ ጎሳ ወይም መሠሪ ማህበረሰብ
ለአንድ ሀገር ነቀርሳ መሆኑን በውል ተገንዝቧል፡፡ ለአይሁዶች የክፍልፋይ ክፍልፋይ ደቂቃ ግዜ ፋታ ላለመስጠት በተግባር አቋም ታጥቀዋል፡፡
በጀርመን ምድር፤ የህዳጣን /የአይሁዶች/ የኢኮኖሚያዊ ልዕልና ከእንግዲህ ይቆማል…’፡፡ ብዙ የአይሁዶች ቤተ እምነቶችና ምኩራቦች
በጀርመን ህዝብ እንደ ወደሙና እንደተቃጠሉ ይዘረዝርና … ‘ይህ ውጤት በጀርመን ህዝብ ትግል ተመዝግቧል’ ይላል አስኳል ጋዜጣ፡፡
የአስኳል ጋዜጣው መጣጥፍ ይቀጥላል፤ ‘…. የጀርመን ህዝብ ተአምር
ሰርቷል፡፡ ለሁለንተናዊ ህይወቱ መጫጫት አይሁድን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ ህዝብ ባመነበት አቅጣጫ ለማምራት ባለመብት ነው፡፡ ማን ይጠይቀዋል?
የጀርመን ህዝብ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በየትም ሀገር የአንድን ጎሳ ወይም ማህበረሰብ ለማስወገድ የህዝብ ተሳትፎ የግድ መሆኑን ተጨባጫዊ
ያደርጋል፡፡ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ተወደደም ተጠላም፤ በህዝብ ተሳትፎ ይካሄዳል፡፡ በመሆኑ ሕዝብን ወደ ጎን በመተው አንድን ፓርቲ
ወይም ቡድን ተጠያቂ ማድረግ ሐቅን መሸፋፈን ነው፡፡ ዕውነትን መደበቅ ሆኖ ይመዘገባል፡፡ ዘር የማጥፋት ዘመቻ ሁልግዜም፤ በይዘታዊ
ተልዕኮው የሕዝብን አቋምን ይወክላል፡፡ አንድ ነቀርሳ ዘር ጐሳ ወይም ማህበረሰብ ከየትም ሀገር መደምሰስ አለበት፡፡ የሀገር ህልውና
በዚህ መልኩ እንዲከበር የግድ ሲል ይፈጸማል…’ ይላል፡፡
ሁለተኛው ቃየን አቶ መሳይ መኰነን ነው፡፡ አቶ መሳይ መኰነን፤
በ2009 (Sept
4/2016)
የትግራይ ህዝብ ለማስጠቃትና ለማጥፋት ከመስበክ በቀር ሌላ ዓላማ ባላነገበ የተሌቪዥን ሚዲያ፤ በእሳት ሳትላይት ተሌቪዥን መስኮት
ላይ ብቅ ብሎ፤ የዘር ማጥፋት መግለጫ አቅርቦ ነበር፡፡ ይህ የዘር ማጥፋት ጥሪም በሰላማዊ የትግራይ ህዝብ ያነጣጠረ ነው፡፡ የአቶ
መሳይ መኰነን የዘር ማጥፋት ጥሪ መግለጫ ላይ፤ እንዲህ የሚል ይገኝበታል፡፡ “እንደምታዩት እኛን የገጠመን ትግል በማንኛውም ዓለም
እንደሚከሰተው ‘በጨቋኝ መንግስትና በተጨቋኝ ህዝብ’ ተብሎ በሚጠራ መካከል ሳይሆን ‘በአንድ ዘራችሁን በማጥፋት የበላይ ሁኜ ልግዛ’
በሚል ጐሳ እና ፍዳው አላልቅ ባለው ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ነው፡፡ …ይህ የጥፋት ዕቅድ የታቀደው ከ5 ሚልዮን ህዝብ ለ95
ሚልዮን ህዝብ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የህሊና እና የሆድ እስረኞችን እንደ አቶ ሃ/ማርያም ደሳለኝና መሰሎቻቸውን በመጠቀም ነው፡፡
…. ወደድንም ጠላንም ምርጫው አንድ ብቻ ነው፡፡ እነሱ ወደ ፈለጉት የሃይል እርምጃ በመግባት ነጻነትን ማስመለስ፡፡ የተበላሸን
ዓሳን ከባህር ማስወገጃ መንገዱ አንድ ነው፡፡ የባህር ውሃ ማስወገድ…”
ሦሥተኛው ቃየን የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ አባል የነበረ አቶ
አናንያ ሶሪ ነው፡፡ ሬድዮ ፋና በመጓች ፕሮግራሙ፤ በኢትዮጵያ ስለተከሰተ የብሔር ግጭት እንደአጀንዳ በማቅረብ ግለሰቦች ያላቸው
አረዳድ ለማንጸባረቅ ማለትም በኢትዮጵያ ስለተፈጠረ ግጭት መንስኤውና መፍትሔው እንደቡድን እንዲወያዩና እንዲከራከሩ መድረክ ከፍቶ
ነበር፡፡ በዚህ መሰረት፤ በፕሮግራሙ የተጋበዙ ግለ ሰቦች፤ በወቅቱ በትግራይ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ስላለ ጥቃት በተለይ ደግሞ በ2008
ዓ.ም በጎንደር ላይ በትግራይ ህዝብ ላይ ስለደረሰ ጥቃት እንደአብነት በማንሳት፤ ተከራክረዋል፡፡ በግልጽ እንደአንድ አጀንዳ የቀረበው፤
ከላይ የተገለጸው በእሳት ሳትላይት ተሌቪዥን ላይ በአቶ መሳይ መኰነን የተሰጠ የዘር ማጥፋት መግለጫ ነበር፡፡
አቶ አናንያ፤ በትግራይ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ስላለው ጥቃት
በተለይ በጎንደር ላይ ስለነበረው ሁኔታ፤ የጎንደር ህዝብ እንደህዝብ፤ በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸመው ድርጊት ትክክል ነው ብሎ ያምናል፡፡
‘…እኔ ማረጋገጥ የምፈልገው… በዚች ሀገር እኮ በይፋ በአማራው ህዝብ ላይ ብዙ ነገር ሲደረግ ኖሯል፡፡ ያንን የተከላከለው ማን
ነው?… ስለዚህ፤ ማንም እንደህዝብ ሲጠቃ በህዝብነቱ ሊቆም ይገባዋል፡፡ ትክክል ነው ያደረገው’ ይላል አቶ አናንያ፡፡ አቶ አናንያ
በማንኛውም ግዜና በየትኛውም ቦታ በአማራ ህዝብ የደረሰው ጥቃት የትግራይ ህዝብ ተጠያቂ ማድረጉ ነው፡፡ ሌላው፤ አቶ አናንያ የጎንደር
ህዝብ፤ እንደአማራ ህዝብ በትግራይ ህዝብ ላይ የወሰደው እርምጃ ትክክል ነው እንዲል የተገደደበት ምክንያት፤ በስርዓቱ ተጠቃሚ የትግራይ
ህዝብ ብቻ እንደሆነ ስለሚያምን ነው፡፡ ‘…ሆን ተብሎ ልዩነት ተኰር ፈደራሊዝምን በማቀንቀን በህዝቦች መካከል ልዩነትንና አድሎ
በማድረግ የተወሰነ ብሔር የበላይነትን ልዕልና የሚያቀነቅን ጠባብ ዘረኛ ቡድን በስልጣኑ ተቆጣጥሮ በልዩነት አያያዝ ስለያዛት ይችን
ሀገር፤ የአንደኛ ደረጃ ዜጋነት እና የተዋረድ የሁለተኛና ሦሥተኛ ደረጃ ዜጋ ስላለ፤ መዋቅራዊ የሆነ፤ ስር የሰደደ፤ ከጅምሩ የተበላሸ፤
ተጣሞ ያደገ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አካሄድ ያመጣው ነው፡፡ ….ሲስተማቲክ በሆነ መንገድ፤ ስልታዊ በሆነ መንገድ የአንድን ዘር የበላይነት
በሚያረጋግጥ መንገድ እየተከተሉት ያሉት ፖሊሲ ሊቀይሩ ይገባል፡፡ ስለዚህ፤ ዋናው መንስኤው ልዩነት ተኰር ፌደራሊዝም ነው’ ብሎ
ያምናል፡፡ አቶ አናንያ አሁን ባለው የንቃተ ህሊና ደረጃ፤ የትግራይ ህዝብና ህወሐት መለየት ያቃተው ይመስል፤ የትግራይ ህዝብ ጥቃት፤
የህወሐት ተግባር ውጤት እንደሆነ በማመን፤ ህወሐትን ‘የዘራውን ነው እያጨደ ያለው’ በማለት በትግራይ ህዝብ እየተፈጸመ ያለው የጥቃት
ድርጊት ‘ትክክል ነው’ ብሎ ያሰምርበታል (መስከረም 30፤ 2016 ዓ.ም.ፈ በ‘ዩ ቱዩብ’ የተለቀቀ
(https://www.youtube.com/watch?v=s9HRv91HEz4 ይመልከቱ)፡፡
የ2008 ዓ.ም ስለጎንደር የነበረው ሁኔታ አንድ የአማራ ብሔር
ተወላጅ የዩኒቨርስቲ መምህር የተናገረው የላይኞቹ ነጸብራቅ በመሆኑ፤ እዚህ ጽሑፍ ላይ ማካተት ፈለግኩ፡፡ በዲላ ዩኒቨርስቲ መስከረም
2009 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚመሩት በህዝቦች መሃከል እየተፈጠረ ያለው ግጭት ለመፍትሔው ከምሁራን ሐሳቦች ለመሰብሰብ
ነበር፤ የስብሰባው አንዱ ዓላማ፡፡ የመምህሩ ንግግር፤ ረዥም ግዜ የወሰደና እጅግ በጣም አስቀያሚ ሲሆን፤ ለዘብ ባለ መልኩ ባጭር
ዐረፍተ ነገር ሲገለጽ ግን “…በትግራይ ህዝብ ላይ የደረሰው ጥቃት፤ የትግራይ ህዝብ ይገባዋል” የሚል ነበር፤ ምክንያቱ ሲገልጽ
ደግሞ “የትግራይ ህዝብ የወያኔ ደጋፊ ስለሆነ” የሚል ነበር፡፡ እንግዲህ ግለሰቡ እንደምሁር ለግጭቱ መፍትሔ ሲሰጥ፡፡
‘ናዚስቶች’፤ በጀርመን ሃገር ‘የአይሁዶች ልዕልና ጀርመንንና
ጀርመናውያንን ጎዳ’ በሚል ሰበብ በ6 ሚልዮን ንጹሃን አይሁዶች ላይ የጅምላ ግድያ ፈጸሙ፡፡ በሃገራችንም፤ በእስክንድር መሪነት፤
እስክንድርና መሰሎቹ ‘የትግራይ ህዝብ ልዕልና ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ጎዳ’ የሚል ሰበብ ተጠቅመው በ6 ሚልዮን ንጹሃን ተጋሩ ላይ
የዘር ማጥፋት ዘመቻ እንዲካሄድ እያደረጉት ባሉት ጥረት፤ ከ‘ናዚስቶች’ ጋር ቢያመሳስላቸውም፤ በወንድማቸው በትግራይ ህዝብ ላይ
በመነሳታቸው ደግሞ ከቃየን ጋር ያቈራኛቸዋል፡፡ በዓለማዊ ወይም መንግስታዊ ህግ መሰረት፤ ማንም ሰው፤ ሰው በገደለ ግዜ፤ በዝምድና
ምክንያት ወይም በባዳነት ምክንያት ቅጣቱ ሊከብድለት ወይም ሊቀልለት አይችልም፡፡ በሌላ አባባል፤ ማንም ሰው ወንድሙ ስለገደለ ቅጣቱ
ሊከብድ አይችልም፡፡ ማንም ሰው ባዳ ወይም ዘመድ ያልሆነ ሰው ስለገደለ ቅጣቱ ሊቀልለት አይችልም፡፡ ነገር ግን ማንም ሰው የህሊና
ፍርድ ሲሰጥ፤ ወንድሙ በገደለና ባዳ ወይም ዘመድ ያልሆነ ሰው በገደለ ላይ እኩል ፍርድ አይሰጥም፡፡ ዳኛ ይሁን የመብት ተሟጓች፤
ሃገር መሪ ይሁን መናኝ፤ በእነዚህ ሁለት ሰዎች ላይ ስለገዳይነታቸው፤ እኩል ስሜት አይኖራቸውም፡፡ ማንም ሰው በግለ ሰብ ደረጃ
እኩል የሆነ ህሊናዊ ፍርድ አይሰጥም፡፡ ይህ፤ ተሽቀንጥሮ የማይጣል መንፈሳዊነት ወይም ህሊናዊነት ነው፡፡
በዓለማዊ ህግ በእኩልነት የተፈረጁ መጥፎ ድርጊቶች፤ ህሊናችን
ሰፊ ልዩነት ይፈጥርባቸዋል፡፡ በዓለማዊ መስፈርት በእኩልነት የተፈረጁ በጎ ነገሮችም፤ ህሊናችን ሰፊ ልዩነት ይፈጥርባቸዋል፡፡ ህሊናችን፤
ከዓለማዊ ወይም ከመንግስታዊ ህግ የበለጠ የነገሮች መጥፎነት ወይም በጎነት አርቅቆ በመርመር ተገቢ ዋጋቸው ይሰጣል፡፡ የተፈጥሮ
ህግም ተመሳሳይ ፍርድ ሲሰጥ ይታያል፡፡ ለአብነት ቃየን ወንድሙ በገደለ ግዜ፤ የአቤል እግዝሔር አስቆጣ፡፡ ቃየን የእግዝሔር መርገምና
ኩነኔም አልቀረለትም፡፡ እንግዲህ፤ ህሊና በተፈጥሮ ህግ ቁጥጥር ስር መሆኑ ነው፡፡ ዓለማዊ ህግም በጎ ይሁን መጥፎ ግላዊነትን መቆጣጠር
በሚያስችልና ህዝቦችን ሊያግባባ በሚችል ስምምነቶች የታሰረ ቢሆንም፤ መንስኤው የተፈጥሮ ህግ ነው፤ ከተፈጥሮ ህግ ውጭም መሆን አይችልም፡፡
ህሊናችን እናቱ ወይም አባቱ ወይም ወንድሙ ወይም እህቱ ለገደለ
ሰው፤ ለምን የበለጠ ቅጣቱ ያከብድለታል? ጤነኛ አእምሮ ያለው ማንም ሰው፤ ሰው ተፈጥራዊ ባልሆነ እንዲሞት ወይም እንዲገደል የማይፈልግበት
ምክንያት፤ አንድም፤ ከሃይማኖታዊና ባህላዊ ህጎች ስለመጥፎና በጎ እምነቶች በሂደት ያዳብርና መጥፎ ድርጊቶች ስለሚጸየፍ፤ ወይም
የሰው ልጅ ከህገ መንግስታትና ሌሎች ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች ስለሰው ክቡርነት ንቃተ ህሊናው ከፍ ያደርግና ‘ሰው የመኖር መብት
አለው’ የሚል የእምነት ደረጃ ሲደርስ ነው፡፡ ሌላው፤ ሰው መግደል የህግ ጥሰት ስለሆነ ማንም ከራሱ ሂወት ጋር በማያያዝ ስለሚፈራ
ነው፡፡ ነገር ግን እናቱ ወይም አባቱ ወይም ወንድሙ ወዘተ ለገደለ ሰው ህሊናችን የበለጠ ይኰንነዋል፡፡ ለምን ቢባል፤ ማንም ሰው፤
ከቤተ ሰብ አባላት ቁሳዊና መንፈሳዊ ውለታዎች አሉበት፡፡ እነዚህ ውለታዎች፤ ከቤተ ሰብ አባላት ጋር ጥብቅ የሆነ የመንፈስ ቁርኝትና
ፍቅር ይፈጥርለታል፡፡
በሌላ በኩል፤ እነዚህ የቤተ ሰብ መንፈሳዊ ስጦታዎች አንድን
ሰው ሰዋዊ ባህርዩ እንዲጎላ ያደርጉታል፡፡ በመሆኑ፤ ወንድሙ ወይም አባቱ ወይም እናቱ ለመግደል ይነሳሳል ተብሎ አይገመትም፡፡ በሌላ
አባባል፤ እናቱ የገደለ ሰው የሌሎች እናቶች ወይም ሌላ ማንም ሰው ከመግደል የሚኰንነው ሰብአዊ ሞራል አይኖረውም፡፡ አባቱና ወንድሙ
የገደለም እንዲሁም፡፡ ስለዚህ፤ የወንድሞቻቸው የትግራይ ህዝብ መጥፋት የተመኙ እስክንድርና መሰሎቹ፤ ከ‘ናዚስት’ ይልቅ ‘ቃየን’
የሚል የበለጠ ይገልጻቸዋል፡፡ ናዚስቶች ቃየንን የመሆን ዕድል ላይኖራቸው ይችላል ምክንያቱም ናዚስቶች ‘ጀርመኖች ናቸው’ ብለው
ያመኑባቸው ወንድሞቻቸውን አልነኩም፡፡ ቃየን ግን ናዚስት ከመሆን የሚከለክለው የለም ምክንያቱም ወንድሙን የገደለ ቃየን ሌላው ከመግደል
አይመለስምና፡፡
የኢትዮጵያ ቃየናውያንም፤ ወንድሞቻቸው ብቻ ሳይሆን እናቶቻቸው፣
አባቶቻቸውና ህጻናት ልጆቻቸው ለማስገደል፤ የትብብር ጥሪ ሲያቀርቡ ሌላው ለመግደል የሚያግዳቸው አይኖርም፡፡ እዚህ ልብ ሊባል የሚገባው
ጉዳይ፤ የጤናማ ሰው ህሊና ለተፈጸሙ ድርጊቶች እንደየክብደታው የሚሰጠው መልስ ለማስገንዘብ እንጂ በሰው ልጅ የሚፈጸሙ የክፋት ድርጊቶች
አንዱ ከሌላው ይሻላል ተብሎ ዕውቅና ለመስጠት አይደለም፤ በማንኛውም ሰው የሚፈጸሙ መጥፎ ድርጊቶች ልዩነት ሳይፈጠር ሊኰነኑ እንደሚገባ
የማንም ጤነኛ ሰው እምነት መሆኑን ሊዘነጋ አይገባም፡፡
በፋና ሬድዮ ከአቶ አናንያ ጋር የክርክሩ መድረክ ተሳታፊ የነበረው
አቶ ፋኑኤል ‘ፌደራሊዝሙ የትግራይ ህዝብ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተቀረጸ ነው፤ የትግራይ ህዝብ ልዩ ተጠቃሚ ነው፤ ስለዚህ የጥቃቱ
ሰለባ ቢሆንም ይገባዋል’ የሚል የአቶ አናንያና መሰሎቹ አስተሳሰብ በመቃወም ይሞግታል፤ እንዲህ በማለት…
“ህወሐት ፖለቲካ ፓርቲ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም
ህዝብ ነው፡፡ ….ህወሐት በትግራይ ህዝብ ማህበራዊ መሰረት የበቀለ ፖለቲካዊ ፓርቲ አሁንም የትግራይ ህዝብ ‘ይወክለኛል’ ብሎ ድጋፍ
የሰጠው ነው እንጂ፤ ለትግራይ ህዝብ በዚች ሃገር ለመቀጠልም፤ ወደፊት ለመራመድ የህወሐት ዋስትና አያስፈልገውም፡፡ ህወሐት ነገ
በትግራይ ህዝብ ማህበራዊ መሰረት ላይ የማይቆም አናርኪ ስርዓት ከሆነ፤ የትግራይ ህዝብ፤ (ህወሐትን) የማይጥልበት ምንም ዓይነት
ምድራዊ ምክንያት የለውም፡፡ ስለዚህ፤ ተጠቃሚነት ስንል በፖለቲካዊ ፖርቲዎች ባራቱ ፖለቲካዊ ፖርቲዎች ውስጥ ‘የህወሐት ባለስልጣናት
ትልቅ ስልጣን ይዘዋል’፤ ያ የኢህአዴግ ችግር ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ችግር አይደለም፡፡ ኦፒዲኦ (OPDO)፣ ብአዴንና ደቡብ ህዝቦች
ታግለው ስልጣናቸው እንዲከፋፈሉ፡፡ ህዝቡ ግን እንደህዝብ ‘ሌላውን ላይ የበላይ ነው፤ የተለየ ተጠቃሚ በሆነ መልኩ ነው ህገ መንግስቱ
የረቀቀው ወይም ህዝቡ ተጠቅመዋል’ የሚባለው ነገር ተቀባይነት የለውም፡፡ የማይካደው ምን አለ፤ ስርዓቱ እየተጣቡ ከመንግስት ባለስልጣን
ጋር ሆነው ሚልየነር፤ ቢልየነር ይሆናሉ፤ የአደባባይ እውነት ነው፡፡ እሱ የማይሰረቅ ሲስተም ገንብተን እንጂ ህዝቡ ተቆጥተን አይደለም”፡፡
ሁሉ እንደ አቶ ፋኑኤል ቢሆን ኖሮ፤ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ጥፋት
ባልደረሰ ነበር፡፡ እነ እስክንድር ሆኑ አቶ ፋኑኤል፤ የትግራይ ህዝብ በምን ደረጃ እንዳለ ሐቁን ያውቁታል፡፡ አቶ ፋኑኤል ከነ
እስክንድር በተለየ መልኩ፤ ሐቁን መከተሉ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡
The Organization of Tigrian’s Network
for the Affirmative Action (OTNAA, 2016) የተባለ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት፤ የአቶ መሳይ መኰነን
በእሳት ሳትላይት ተሌቪዥን፤ በትግራይ ህዝብ ላይ ያቀረበው የዘር ማጥፋት ጥሪ፤ በሰለጠነ ዘመን፤ የሰው ልጅ ከፈጸመው፤ “…ከሁሉም
የከፋ ሰይጣናዊ የወንጀል ድርጊት…” በማለት ገልጾታል
(http://www.aigaforum.com/current-issue/A-Call-of-OTNAA-for-Affirmative-Action.pdf)፡፡
በመሰረቱ ዘር ማጥፋት /genocide/ ማለት ምን ማለት ነው?
በ1948 ዓ.ም.ፈ ስለዘር ማጥፋት የተደረገ አለም ዓቀፋዊ ስምምነት
/Genocide Convention/ አለ፡፡ በዚህ ስምምነት፤ አንቀጽ ሁለት መሰረት፤ ዘር ማጥፋት /genocide/ ማለት ብሔር፣
ጐሳ፣ ዘር ወይም የሃይማኖት ቡድን በመላ ወይም በከፊል ለማጥፋት ሆን ተብሎ የሚፈጸም ማንኛውም ድርጊት ነው፡፡
ለምሳሌ፤ ሀ) የቡድኑ አባላት መግደል፣ ለ) በቡድኑ አባላት
ላይ አካላዊና ስነ አእምሮአዊ ጉዳት ማድረስ እና ሐ) የቡድኑ የህይወት /ኑሮ/ ሁኔታዎችን ሆን ብሎ ለመጉዳት፤ በመላ ወይም በከፊል
የቡድኑ አካላዊ ጉዳት /ቁሳዊ ወድመት/ ማድረስ የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡ እነዚህ ስምምነቶች ዓለም ዓቀፋዊ ቢሆኑም፤ የዓለም መንግስታት
እና የሰዎች መብት ተማጓቾች ድርጅቶች (ከOTNAA በቀር) እና ግለ ሰቦች ድምጻቸው አልተሰማም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም፤ እስክንድር
ነጋ ቢያስረውም፤ ‘ቀጥልበት’ በሚመስል ዓይነት ያለምንም ምክንያት መልሶ ከእስር ለቆታል፡፡
ያም ሆነ ይህ፤ እስክንድርና መሰሎቹ፤ ናዚስቶች (እንደ እስክንድር
አባባል የጀርመን ህዝብ) በአይሁዶች ላይ የፈጸሙት ግፍ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በትግራይ ህዝብ ላይ እንዲደግም ጥሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡
እነዚህ የሃገራችን ‘ቃየኖች’፤ የትግራይ ህዝብ የአይሁዶች ዕጣ ፈንታ እንዲደርሰው ካላቸው ፅኑዕ ፍላጎት የተነሳ፤ የትግራይ ህዝብ
ለማጥፋት፤ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝብ እርዳታ ይጠይቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ያነሳሳሉ፡፡ ከላይ በተጠቀሰው ስምምነት መሰረት ሲታይ፤
ዛሬ በኦሮምያና በአማራ አከባቢዎች፤ የትግራይ ህዝብ የዘር ማጥፋት ጥቃት ተፈጽሞበታል፡፡ ይህ ድርጅት የእስክንድር ነጋና መሰሎቹ
ቅስቀሳ ውጤት ቢሆንም የእነሱ ፍላጎት የሆነውን የህዝቡ ጨርሶ መጥፋት ግን አልተሳካላቸውም፤ ሊሳካም አይችልም፡፡ አንድን ህዝብ
ከገጸ ምድር ጠቅልሎ ማጥፋት እንደማይቻል፤ ዛሬ የአይሆዶች በምድር ላይ መኖር ህያው ምስክርነት እንደሆነ ‘ቃየናውያን’ መገንዘብ
አልቻሉም፡፡ ፍላጎትና ስስት ሁኔታዎች ለማገናዘብ ዕድል አይሰጡምና፡፡
ተወደደም ተጠላም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት አይሁዶች /እስራኤላውያን/
ከዓለም ህዝብ ሁሉ የላቀ ታሪክ አላቸው፡፡ በመሆኑ፤ የግል ጥቅም ለማስጠበቅ በሚኳትኑ በጥቂቶች እየተመራ ከዓለም ህዝብ ብዙ ጥቃቶች
ተሰንዝሮባቸዋል፡፡ የእስራኤላውያን የታሪክ ቅርሶች ለመዝረፍ ወይም ለማጥፋት ከሌሎች ህዝቦች (እንደነሮማውያን የመሳሰሉት) ወረራ
ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ግብጻውያን፤ እስራኤላውያንን (ሙሴ ነጻ እስኪያወጣቸው ድረስ) እንደህዝብና እንደሰዎች ዕውቅና መስጠት ሳይፈቅዱ፤
በባርነት ቀፍድደው እንዲያኖሯቸው ፈልገው ነበር፡፡ በ1967 ዓ.ም.ፈ ‘በስድስት ቀን ጦርነት’ እስራኤላውያን ግብጻውያንን እስክያሸንፏቸው
ድረስ፤ ግብጻውያን የእስራኤላውያን ህልውና ነፍጓል፡፡
ናዚስቶች፤ የአይሁዶች ልዕልና በመስጋት የአይሁዶች ህልውና አልፈቀዱም፡፡
አይሁዶችን በዓለም ላይ እንዲኖሩ አልፈለጉም፡፡ ናዚስቶች፤ ህጻናት፤ እናቶች ወይም አዛውንት ሳይሉ በ6 ሚልዮን ንጹሃን አይሁዶች
ላይ የጅምላ ግድያ ፈጸሙ፡፡ ነገር ግን አይሁዶች ከጀርመኖች ጋር አብሮ መኖር ባይችሉም፤ ጀርመኖች አይሁዶችን ከገጸ ምድር ማጥፋት
አልቻሉም፡፡ እስራኤላውያን አሁን የታሪካቸው መጀመርያ ወይም መነሻ ወደ ሆነችው ሰፈር ወይም ሀገር ወደ እስራኤል ተመልሰው በመግባት
እየኖሩ ነው፡፡ ዛሬም፤ ፍልስጥኤማውያን፤ እስራኤላውያንን ‘አናውቃችሁም’ በማለት ዕውቅና መስጠት ባይፈቅዱም፤ የእስራኤላውያን ህልውና
አላከተመም፡፡ ሆኖም ግን ባለመስማማትና ባለመቻቻል ምክንያት የማያበራ ግጭት ሊፈጠር በመቻሉ የሰው ህይወት መቀጠፍና የንብረት ውድመት
ዘወትር ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡
የትግራይ ህዝብም፤ ከኢትዮጵያ ህዝቦች ለየት ባለመልኩ የውጭ
ወራሪዎች ሰለባ ሆኖ ለዘመናት ቆይቷል፡፡ ምናልባት ህዝቡ የሰፈረበት አከባቢ ‘የጂኦ-ፖለቲክስ’ አቀማመጥ የሰለባው ምክንያት ሊሆን
ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት አከባቢ ወይም ህዝብ፤ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከውጭ ወራሪ ሊከላከልለት ወይም ከጦርነት በኋላ
ቢሆንም ማገገሚያ ሊያበጅለት እንደሚገባ አያከራክርም፡፡ በአንጻሩ ግን የሀገራችን ገዢዎች፤ የትግራይ ህዝብ በባርነት ይፈልጉት ነበር፡፡
ያም ሆነ ይህ፤ የትግራይ ህዝብ ለማንም አልተበገረም፡፡ የትግራይ
ህዝብ፤ የሀገሩ ክብር ለማስጠበቅ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ለአብነት የሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች እርዳታ ሳያገኝ፤ በዘጠኝ ዓመት ውስጥ
ዘጠኝ ጦርነቶች ከውጭ ሃይሎች ጋር በማካሄድ መስዋዕት ሆኗል፡፡ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ በመሆንም ለሀገሩ ትልቅ ዋጋ እንደከፈለ
እሙን ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ የትግራይ ህዝብ ከውስጥ በኢትዮጵያውያን ገዢዎችና ግለሰቦች ጥቃት ሲደርስበት ትላንትም ዛሬም ይስተዋላል፡፡
ለአብነት በአጼ ምንሊክና ሃ/ስላሴ የሰው ልጅ ሊቋቋመው የማይችል ግፍ ይደርስበት ነበር፡፡ ለአብነት በሁለቱ ገዢዎች ግድያና ዘረፋ
እንዳለ ሆኖ፤ የትግራይ ህዝብ ዘር እንዳይተካ በማሰብ ወንዶችን መስለብ የመሳሰሉት እኩይ ተግባሮች ይፈጸምበት ነበር፡፡ ዋጋ ቢያስከፍለውም፤
ለኢትዮጵያውያን ገዢዎችም እነሱ በፈለጉት መሰረት አሜን ብሎ አልተገዛላቸውም፡፡
በደርግ የተካሄደበት የዘር ማጥፋት ዘመቻም ክፉኛ ቢጎዳውም፤
አላጠፋውም፡፡ መልሶ ደርግን አጠፋ እንጂ፡፡ በዘመነ ኢህአዴግም፤ እንደነእስክንድር ነጋና መሳይ መኰነን የመሳሰሉት ‘ቃየናውያን’
የትግራይ ህዝብ ለማጥፋት ቆርጠው ተነሱ፡፡ እስራኤላውያን ‘እስራኤል የእናንተ አይደለችም’ እንደተባለ ሁሉ፤ ዛሬ ይባስ ብሎ የትግራይ
ህዝብ፤ በፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ (2008) የጥንቆላ ታሪክ ተጽፎበት፤ ‘በታላቁ አሌክሳንደር ለኢትዮጵያዊው ንጉስ በስጦታ የተበጀህ
እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለህም’ እየተባለ ነው፡፡ ይህ በትግራይ ህዝብ ላይ ሌላ የጥቃት አቅጣጫ በመፍጠር የግጭት በር ለመክፈት የታሰበ
ይመስላል፡፡ ነገር ግን ሳይውል ሳያድር፤ በቴዎድሮስ ፀጋየ ‘ርዕዮት’ በተባለ ፕሮግራሙ አማካኝነት በዓለም ህዝብ ፊት በሚዲያ ቀርቦ
ውሸትነቱ ተረጋገጠ፡፡ ፍቅሬ ቶሎሳም ሐፍረትን ተከናነበ፡፡
እንደ መፍትሔ
የትግራይ ህዝብ፤ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ‘ልዩ ተጠቃሚ ነው’
ተብሎ በግለ ሰቦች በሚረጭ የውሸት ፕሮፖጋንዳ፤ በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በመጥፎነት እንዲታይ አድርጎታል፡፡
በመሆኑ፤ ብዙ የህይወትና የንብረት ኪሳራ እየደረሰበት ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም እና በ2009 ዓ.ም መጀመርያዎች አከባቢ፤ ከ20,000
በላይ ንጹሐን ተጋሩ ኢትዮጵያውያን የተፈናቀሉ ሲሆን (OTNAA, 2016) ከ4 ሺ በላይ ደግሞ ወደ ሰሜን ሱዳን በመሰደድ ተመልሰው
ወደ ትግራይ መግባታቸው ይታወቃል (የትግራይ TV, 2008) (ወደ ትግራይ ምን ያህል እንደተመለሱ ግን በውል አይታወቅም)፡፡ ይህ
አፋጣኝ መፍትሔ የሚያስፈልገው ጉዳይ ሲሆን ቢያንስ ሦሥት የመፍትሔ አካላት ሊሆኑ የሚችሉ አሉ፡፡
የመጀመርያው እና ዋነኛው፤ የፌደራል መንግስት ነው፡፡ በህገ
መንግስታችን መሰረት፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፤ በማንኛውም የሃገሪቱ ክፍል የመዘዋወርና የመኖር መብት አለው፡፡ በማንኛውም የሃገሪቱ
ክፍል ንብረት የማፍራት መብት አለው፡፡ በመሆኑ መንግስት የዜጎቹ ሰውነትና ንብረት የመጠበቅ ግዴታ አለው፡፡ በእነዚህ መስፈርቶች
ቀለል ባለ መልኩ፤ ዛሬ በሃገራችን የመንግስት ድርሻ ስንገመግመው፤ ህገ መንግስቱ መሰረት በማድረግ መፍትሔ መስጠት አልቻለም፡፡
በግጭቱ ምክንያት ዜጎች ሲሞቱ እና ብዙዎች በተፈናቀሉና ንብረታቸው በወደመ ግዜ፤ የመንግስት ሚና፤ የኳስ ዳኛ በሜዳ ላይ የሚጫወተው
ሚና ያህል አልነበረውም፡፡ ግጭት የተፈጠረበት ቦታ እየዞረ፤ ስለግጭቱ ለህዝብ ከማሳወቅ በቀር የሰራው ስራ የለም፡፡ ስለዚህ፤ በመጀመርያ
መንግስት በሰዎች ሂወትና ንብረት ጥቃት እንዳይደርስ መጠበቅ መቻል አለበት፡፡ ሲፈጸምም የመፍትሔ አካል በመሆን መንግስታዊ ግዴታው
ሊወጣ ይገባል፡፡
ሁለተኛው፤ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ወይም ምክር ቤት ነው፡፡
የትግራይ ክልላዊ መንግስት መንግስታዊ ግዴታው ቢዘነጋም፤ ያለ ትግራይ ህዝብ የክልሉና የፌደራል መንግስት መሆን እንደማይቻል መገንዘብ
ይኖርበታል፡፡ ያለትግራይ ህዝብ፤ ከኦህዴድና ብአዴን ጎን ቁጭ ማለት እንደማይቻል ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑ፤ የትግራይ ክልላዊ
መንግስት ወይም ምክር ቤት ለህልውናው ሲል የትግራይ ህዝብ ድህንነት ያለይሉኝታ መጠበቅ ይኖርበታል፤ ለትግራይ ህዝብ ዘላቂ መፍትሔ
ሊያመጣለት ይገባል፡፡
ሦሥተኛው፤ የትግራይ ህዝብ ራሱ እንደህዝብ የመፍትሔ አካል መሆን
እንደሚችል ጠቋሚ አያስፈልገውም፡፡ ያለፉ የኢትዮጵያ ገዢዎች/መንግስታት ለትግራይ ህዝብ በነፍጥና በቦምብ አጋዩት እንጂ ዳቦ አላመጡለትም፤
መከራና ሰቀቀን ይጋብዙታል እንጂ አለኝንታ የሆኑበት ግዜ እምብዛ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ፤ ይደርሱበት ከነበሩ የተለያዩ ችግሮች፤
እንደህዝብ ራሱ የመፍትሔ አካል በመሆንና ራሱ እየታገለ ከችግሮቹ የተላቀቀበት በርካታ ግዜያቶች እንደነበሩ ያለፈ ታሪኩ ይመሰክራል፡፡
ስለዚህ፤ የትግራይ ህዝብ፤ ለሚደርሱበት ችግሮች ሊያስወግድ የሚችል የትግል አቅጣጫ በመቀየስ፤ ለዘላቂ መፍትሔ ዛሬም እንደ ትላንት
ሊታገል ይገባል፡፡
*******
(ገ/መድህን ሮምሃ (ዶ/ር)
No comments:
Post a Comment